አለቃ ገብረሐና
እና
አስቂኝ ቀልዶቻቸው

በ አረፈ ዓይኔ ሐጎስ ……… አዲስ አበባ መጋቢት 1977
ማውጫ
አርእሰት
መግቢያ
ምእራፍ አንድ ፤ ከልጅነት እስከ አጫዋችነት
ምእራፍ ሁለት ፤ ቀልድ በዛ ፣ ስደት ተከተለ
ምእራፍ ሶስት ፤ ከስደት ወደቤተ መንግስት
ምእራፍ አራት ፤ ድንግልና ፈረሰ
ምእራፍ አምስት፤ የትዳር ዓለም
ምእራፍ ስድስት፤ በስተርጅና ስደት
ምእራፍ ሰባት ፤ ” ሞቼ ተነሳሁ “
ምእራፍ ስምንት፤ ኩርፊያ ወይስ ንስሃ ?
መግቢያ ::
ደስታ ተክለወልድ አጫዋች የሚለውን ቃል ሲፈቱት ” የሚያጫውት ፣ አነጋጋሪ ፣ አስቂኝ ፣ ጥርስ የማያስከድን ፣ አለቃ ገብረሐናንና አባ ምን ይዋብ ከሉን የመሰለ የጨዋታ ፈላስፋ “ ይሉታል:: ቀልዱን ሁሉ ሰብስቦ ላንድ ታዋቂ ሰው መስጠት ወይም ማውረስ የተለመደ ስለሆነ ነው እንጂ አገራችን የነበሩት አስቂኝ ሰው አለቃ ገብረሐና ስለሆኑ ብቻ አይደለም “አለቃ ገብረሐና እንዲህ አሉ” እየተባለ የሚወሳው:: ከጨዋታ ፈላስፋነታችውም በላይ አለቃ ገብረሐና የፍትሀ ነገስቱ ፣ የመጻሕፍቱና የአቡሻክሩ ሁሉ አዋቂ ነበሩ:: ” አለቃ ገብረሐና እጅግ የተማሩ የጎንደር ሊቅ ነበሩ::” ሲሉም ብላታ ህሩይ ወ/ ሥላሴ ይህንኑ መስክረውላቸዋል ::
ይሁንና አለቃ ገብረሐና በዘመናችን የሚታወቁት በምሁርነታቸው ብቻ ሳይሆን በሃይለ ቃላቸውና በቀልዳቸው ነው:: በርግጥም አለቃ ገብረሐና ተረበኛ ፣ ብልህና ጥርስ አያስከድኔ ነበሩ :: በዚህች መጽሐፍ ከሞላ ጎደል የኒህን ሰው ሕይወት ከነመቼቱ ልብ ወለድ በሆነ መልክ ለማሳየት ይሞክራል :: አቀናባሪው አለቃን አያውቃቸውም :: ቢሆንም ስለኒህ ሰው መለስተኛ ጥናት አካሂዷል :: በጥናቱም ወቅት መጀመሪያ ያገኘው የ አበበ አይቼህን ” ቢልጮ ( 1948 ) ” ነበር:: አበበ አይቼህ በዚህ መጽሐፋቸው የ አለቃ ገብረሐና የተባሉና ሌሎችንም አገረኛ ቀልዶችን ተራ ቁጥር በማስያዝ ደርድረው አሳትመው ነበር :: በ አስራዘጠኝ መቶ ሃምሳዎቹ መጨረሻ እንዲሁ ” ሰምና ወርቅ አማርኛ እስኪ እንወቅ “ በተባለው መጽሐፍ ጥቂት የ አለቃ ገብረሐና የተሰኙ ቀልዶችን ከሌሎች ደባልቀው አንድ ሌላ ደራሲ አውጥተዋል ::
የ አለቃ ገብረሐናን የሕይወት ታሪክና ቀልዶቻቸውን ኪናዊ ውበት በመስጠት ” ታሪካዊ ልብ ወለድ “ በሚመስል መልኩ ለማውጣት በማድረግ ረገድ ግን ይህ የመጀመሪያው ይመስለኛል :: በርግጥ ወይዘሪት ኤልሳቤጥ ገሠሠ ከ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመመረቂያቸው ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ” በ አለቃ ገብረሐና የሚነገሩ ቀልዶች “ በሚለው ርእስ በዘገቡት ጽሑፍ የ አለቃ ገብረሐናን የ ሕይወት ታሪክ በጥቂት ገጾች አካተው ከፍ ብለው ከተጠቀሱት መጻሕፍት ባልተለየ መልክ የ ቀልድ ጥርቅሞችን በተራ ቁጥር በመደርደር ያቀረቡት ማለፊያ ጥናት ወረቀት በ ኢትዮዽያ ጥናትና ምርምር ኢኒስቲትዩት ይገኛል ::
ቢሆንም አቀናባሪው ከፍ ብሎ ከቀጠቀሳቸው ምንጮች ያገኛቸውን መረጃዎች ከሰበሰበ በኋላ የተለያዩ ሰዎችን አነጋግሯል ፤ የታሪክ መዛግብትን አገላብጧል ፤ ግለሰቦች የላኩትን ተጨማሪ ቀልዶች መዝኗል ፤ ለጽሑፍ ሥነ ጽሁፋዊ ውበት ለመስጠት ምናቡን ወደዃላ መልሶ ለ አለቃ የሕይወት ታሪክ መቼት በመፍጠር አንባቢ በሕይወት ሲመላለሱ እንዲያያቸው ለማድረግ ሞክሯል ::
ለዚህ ሥራ መሳካትም አፈሊቅ አክሊሉ ገብረኪሮስ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አድርገዋል :: አቶ ተክለጻድቅ መኩሪያና ደራሲ ሐዲስ አለማየሁም እንዳስፈላጊነታቸው ተጠቅሰዋል :: ከሁሉም በላይ ስንፍናና የሥራ ጫና በተጫጫነኝ ቁጥር ውጥኔን እንዳልረሳ ከመጀመሪያው ጀምሮ ያበረታቱኝን አቶ ተስዬ አያሌውን ከልብ አመሰግናቸዋለሁ :: በህትመት በኩልም ለረዱኝ ለ አቶ አክሊሉ ደጀኔ ገዳ ከፍተኛ ምስጋና አቀርባለሁ ::
አረፈ ዓይኔ ሐጎስ
ሐምሌ ፤ 1977 እ.ኤ.አ
አለቃ ገብረሐና ( ምእራፍ አንድ )
ከልጅነት እስከ አጫዋችነት
ገብረሐና ደስታ ተገኝ በደብረታቦር አውራጃ ፎገራ ወረዳ ፣ ናባጋ ጊዮርጊስ በምትሰኝ ስፍራ በ1814 ዓ.ም መወለዳቸው ይወሳል ። ከፍ እንዳሉ ቄስ ትምህርት ቤት ገብተው በፊደል የጀመሩትን ትምህርት ወደዳዊት አዝልቀውት ዜማ ቤት ጥቂት ከቆዩ በኋላ ወደ ጎጃም በመሄድ ከዚያው የቅኔ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ ። ከዚያም ጎንደር ተመልሰው ሙሉ ጸዋትወ ዜማን ፤ አቋቋምን ፤ ድጓንና የመጻሕፍት ትርጓሜን ተማሩ ። የመጻሕፍት ትርጓሜን ያስተማሯዋቸው አቃቤ ስብሃት ገብረመድህን ናቸው ይባላል ። ገብረሐና ትምህርታቸውን እነደጨረሱም ” የኔታ እንግዲህ ይሞክሩና ያሰናብቱኝ “ ቢሏቸው ፤ ” ምን ቀረህ ብለህ ነው? ሁሉን አውቀሃል ፤ ብቻ የደናቁርት ጓደኛ አትሁን ! ” በማለት መከሯቸው ። የዚህን ምክር ጠቃሚነት የተገነዘቡት ገብረሐናም አዲስ መምህር መጣ ተብሎ ወደ ተወራበት አካባቢ ሁሉ ይሄዱ እንደ ነበረ አዋቂዎች ይናገራሉ ። ደቀመዛሙርቶቻቸውንም ” የሰው ቀለም አትናቁ ፤ ሰው ያመጣውን ሁሉ አትንቀፉ “ እያሉ ይመክሩ ነበር ይባላል ።
ተማሪ ገብረሐና በሃያ ስድስት ዓመታቸው ጎንደር ውስጥ ሊቀ ካህናት ሆነው ተሾሙ ። በዚህ ጊዜ አንዲት ጎንደሬ ዘንድ ጠበል ተጠርተው ቢሄዱ የሚመጡት ሰዎች ሁሉ ” ጠላው ጥሩ አይደለም “ ሲሉ ይሰሙና ተመልሰው ወደቤታቸው ይሄዳሉ ። ሴትዮዋም በመቅረታቸው አዝና ቤታቸው ሄዳ ” ምነው አለቃ ጠበል ጠርቼዎት ሳይመጡ ቀሩ ? ብትላቸው ፣ ” አረ መጥቼ ሰው ግም ፤ ግም ሲል ጊዜ ነው የተመለስኩት ” አሉዋት ይባላል ።
አንዲት አጠር ፤ ደልደል ያለች ደባካ መሳይ ጎረቤታቸው ደግሞ ” አባ ሰው ሁሉ ድንቼ ፣ የኔ ድንች እያለ ያቆላምጠኛል ብትላቸው ፣ ” አዬ ሞኝት እውነት መስሎሽ ነው ? ድንቼ ፣ ድንቼ የሚሉሽ ሊልጡሽ እንጂ ነው አሉዋት ።” ከጥቂት ቀናት በዃላም ያችው ገልቱ ሴት ምሳ ትጋብዛቸዋለች ። ሊቀ ካህናት እግራቸውን አንፈራጠው ዶሮአቸውን ሲኮመኩሙ የዶሮው ጭንቅላት ድስቱ ውስጥ እንዳለ ዓይኑ ፈጦ ታያቸው ። ይኸኔ አጅሬ ሳቅ ብለው ፣ ” ዶሮ ምን እኔ ላይ ታፈጥብኛለህ ? እኔ አላረድኩህ “ አሉት ። ገበታው ከፍ እንዳለም ጠላ ቀርቦላቸው ሲጠጡ ቢያጣጥሙት ቀጭን ሆነባቸው ። ታዲያ ይህንኑ እያቅማሙ ሳሉ ሴትዬይቱ መጥታ ” አረ ጠጡ አንድ ተይዞ ቁጭ አይባልም “ እያለች ብታጣድፋቸው ፣ እሺ እጠጣለሁ ። ለመሆኑ ይህን እህል ውሃ ያደረግሺው አንቺ ነሽ ? አሉዋት ።
ሰንበት ብላ ደግሞ ድንቡሼዋ ጎረቤታቸው አዲስ ልብስዋን ልታስመርቅ እየሮጠች ወደ ቤታቸው ስትመጣ አመለጣትና መዓዛው ቤቱን አወደው ። አባ ገብረሐና ግን እንዳላወቀ ሰው “ በውሃ ይለቅልሽ ፣ ጥሎሽ ይሂድ ” ብለው ከመረቋት በኋላ ” እንግዲህ ይህችን ከሰው ዘንድ ስትደርሽ ብን እያደረግሽ ኩሪ ” ብለው አሰናበቷት ። ድንቡሼ ላቅመ ሔዋን እንደደረሰች አንድ አህያ ነጂ አገባች ። ታዲያ ገብረሐና ይንቁት ኖሮ አንድ ቀን ሰውየው አህዮች እየነዳ ባጠገባቸው ሲያልፍ ” ጤና ይስጥልኝ አባ ” ብሎ የግዜር ሰላምታ ያቀርብላቸው ” እግዚአብሔር ይመስገን ። እንደምን ዋላችሁ ? ” በማለት መለሱለት ። አህያ ነጂውም ተበሳጭቶ ነበርና ቤታቸው እስኪገቡ ጠብቆ ገላጋይ በሌለበት ቀጠቀጣቸው ። ዱላው ክፉኛ ጎድቷቸው ስለነበርም ታመው ተኙ ። አመሻሹ ላይ እያነከሱ ከውጭ ሲመለሱ አህያ ነጂው ድንቡሼን አስከትሎ እንዳላወቀ ሰው ሊጠይቃቸው መጣ ። ” አባ ምን ሆኑ ? ” ሲልም ጠየቃቸው ። እሳቸውም ፈጠን ብለው ” አህያ ረገጠኝ “ አሉት።
ያህያ ነጂውን ያክል የሚጠሉት አንድ ፉንጋ ቄስም ነበረ ። ታዲያ ቄስ ሆዬ የ አባ ገብረሐናን ሸፋፋነት ያውቅ ኖሮ ” አባ ሽፍን ጫማ በሸዋ በኩል መጥቷል ይባላልና እንዳያመልጥዎ ” ሲል ያሽሟጥጣቸዋል ” አባ ግን በነገር የሚቀድማቸው የለምና ” አንተ ፊት ግዛና ” ብለው ኩምሽሽ አደረጉት ።
አንድ ባለውቃቢና አጉሪ ደግሞ ሰናይ ምግባር እንደፈጸመ ሁሉ አዲስ ቤት መስራቱን ምክንያት በማድረግ አባን ግብዣ ይጠራቸዋል ። ስራው ያሳዘናቸው አባ ገብረሐና ግን የቀረበውን ሁሉ በደንብ በልተው ዙሪያ ገባውን ከጎበኙ በኋላ ” ቤትህ ካለ ሁለት ነገር የጎደለው የለም “ አሉት ። ባለውቃቢውም በጉጉት ምንና ምን? ብሎ ቢጠይቃቸው ፣ ” ከዚህ በታች ጋጥ ፣ ከዚህ በላይ አጉራ “ አሉት ። ይኸው ባለውቃቢ ፣ ፈረስ ገዛና ፈረሱን እየኮረኮረ ጨርቁን እንደተከናነበ ሲጋልብ አባ ገብረሐናን አገኛቸው ። እዚያው እንደተቀመጠም ” አባ ይመርቁኝ አዲስ ፈረስ ገዝቼ እየጋለብኩ ነኝ “ አላቸው ። አባም “ ጥሎህ ይሂድ ! ጥሎህ ይሂድ! ልጄ “ ብለው መረቁት ።
ከአባ ገብረሐና ፈንጠር ብላ የምትኖር አንዲት ችግረኛ ሴትም ነበረች ይባላል። ይህች ሴት በችጋር ስትሰቃይ እንደኖረች ሞት አይቀርምና አንድ ቀን አረፈች ። አባ ወደ ቤታቸው ሲገቡም ጩኸት ስለሰሙ ” ምንድን ተፈጠረ? “ ብለው ጎረቤት ቢጠይቁ ፣ ” ሴትዮዋ ሞቱ “ አሏቸው ። “ የትኛይቱ ?”… ” እኛ ችግረኛይቱ “….” አሄሄ ፣ ተኖረና ተሞተ “ አሉ አባ ገብረሐና ።
አባ ገብረሐና በሊቀካህናትነት ያሳለፏቸውን ሰባት ዓመታት በስብከት ችሎታቸውና በቀልድ አፍላቂነታቸው ተወዳዳሪ የሌላቸው መሆናቸውን ማረጋገጫ ( ማስማስከሪያ ) ጊዜ አድርገዋቸዋል ። ዳሩ ግን ከንግግር አዋቂነታቸውም በላይ ፍትሐነገስቱን ከተካኑት ምሁራን አንደኛው ስለነበሩ የዳኝነት ሹመት ተሰጣቸው ። የሥራው ጠባይ ስለማይፈቅድላቸው ሳይሆንም አይቀር በዚህ ወቅት ከቀልዱ ቆጠብ ብለው ነበር ይባላል ። አልፎ አልፎ የሰነዘሩዋቸው ጨዋታዎች ቢኖሩም ሕዝብ ዘንድ ሊደርሱ እንዳልቻሉ ይገመታል ። ይህም ሆኖ ስማቸው እየገነነ ስለመጣ የትንሹ ራስ አሊ አጫዋች እንዲሆኑ ተደረገ ። ለ አባ ገብረሐና ይሄ ሙያ ሳያስደስታቸው እንዳልቀረ በቀላሉ መገመት ይቻላል ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ነው ገብረሐና የመንደር ቀልደኛ መሆናቸው ቀርቶ ነገሥታቱን የሚያስቁ ፣ መኳንንቱን አፍ የሚያስይዙ ፣ ካልመሰላቸውም ነገሥታቱን የሚጎነትሉ የምሁር ተረበኛና ቀልድ አፍላቂ ሆነው የኖሩት ።
ትንሹ ራስ ዓሊ ዘንድ በነበሩባቸው ዓመታት የሰነዘሩዋቸውም አብዛኛዎቹ ቀልዶች ተወርተው የቀሩ እንጂ በወጉ ያልተመዘገቡ በመሆናቸውና ይልቁንም ከብዙ ዓመታት በፊት የተወሱ መሆናቸውና ” እንዲህ ብለው ነበር ይባላል “ እያለ እንኳ መተረክ የሚችል ሰው በሕይወት አለመኖሩ ይህን ዘመን በገብረሐና ሕይወት ውስጥ ” የጨለማ ዘመን “ ሊያስብለው ይችላል ። ይህም ቢሆን ፣ አባ ገብረሐና ያፈለቋቸው ቀልዶች ዘመናትን ዘልቀው ለትውልዳችን መድረላቸው አልቀረም ።
የማስተዋል ችሎታቸው ከንግግር ውበታቸው ጋር የተቀናጀው አባ ገብረሐና ባገራቸው ከነበሩት ባህሎች ባንደኛው ቅር ተሰኝተው ይኖሩ ነበር ። ያባት ሆኖ በጎንደር መጠጥ ሲጠጣ አሳላፊው ቁሞ የሚጠጣው ሰው ብርሌውን ባጎደለ ቁጠር እየተጠባበቀ በላይ በላዩ ይቀዳለታል ። ታዲያ አባ ገብረሐና ከእንዲህ ዓይነቱ ግብዣ ሲወጡ አንዱ ” ስንት ብርሌ ጠጡ ?” ብሎ ቢጠይቃቸው ፣ ” ዘጠኝ አንገት ጠጣሁ “ አሉት ይባላል ።
የኝህ ጥርስ አያስከድኔ ጨዋታ ያነሆለላቸው አንድ ደጃዝማች አባ ገብረሐናን ወዳጅ ያደርጓቸዋል ። በየጊዜው ቤታቸው እየወሰዱም ያበሏቸዋል ፣ ያጫውቷቸው ነበር ። እንደተለመደው አንድ ቀን ራት ጋብዘዋቸው ጮማ እየቆረጡ ሲያወጉ ደጃዝማች ግብዣውን ያሳመሩ መስሎአቸው “ይብሉ እንጅ ፣ ሰው እኮ ደስ የሚለው የደገሰውን ሲበሉለት ፣ የወለደውን ሲስሙለት ነው “ ቢሏቸው ፣ አባ ብድግ ብለው የደጃዝማቹን ቆንጅዬ ልጅ ሳም፣ ሳም ፣ ደጋግመው ሳም አደረጓት ። ” ምነው አባ ?” ብለው ቢጠይቋቸው ፣ ” ጌታዬ ምግቡን እስኪበቃኝ ተመገብሁ ። የወለደውን ሲስሙለት ደስ ይለዋል ስላሉኝ ደግሞ ለርስዎ ስል የሚወዱዋትን ልጅዎን ሳምኩልዎ እንጅ አጠፋሁ ? “ በማለት መለሱላቸው ።
ሰኔ ጾም ላይ እንዲሁ ደጃዘማቹ ወዳጃቸው ዘንድ ተጋብዘው ይሄዳሉ ። የጎመን ወጥ ይቀርብናም እንደነገሩ ይጋበዛሉ ። ሆኖም ጎመኑ በደንብ አልበሰለም ኖሮ አባ ሆዳቸውን ይቆዝራቸዋል ። ከግብር መልስም ብርዱ ስላየለ እሳት በእንክርት ወደልፍኙ ቀረበ ። ይኼኔ አባ ገብረሐና ወደ እሳቱ አምርተው በርጩማ ላይ ከተቀመጡ በዃላ ልብሳቸውን ገለጥ አድርገው ሆዳቸውን እሳት ያሞቁ ጀመር ። ደጃዝማቹም በድርጊቱ ተገርመው ” ምነው ሆድዎን እሳት ያሞቃሉ ?” ቢሏቸው ፣ ” ጊታዬ ጎመኔን እያበሰልኩ ነው “ አሏቸው ይባላል ።
ይህን የመሳሰሉትን ቀልዶች እያፈለቁ አገር ያሸነፉትን አባ ገብረሐናን ለማዋረድም የንጉሳውያኑ ቤተሰቦችና መኳንንቱ አንድ ተንኮል ፈጠሩ ። አባ ገብረሐና ግብር ቀርበው እንደተቀመጡም እንደልባቸው መብላት መጠጣት እንደሚችሉ ፣ ሆኖም ወደ ውጭ መውጣት እንደማይፈቀድላቸው ይነግሯቸዋል ። የሚቀርብላቸው ምግብም ጨውና ቅመም የበዛበት ኖሮ በላይ በላዩ ቢጠጡ ሽንታቸው መጣ ። ጨነቃቸው ፣ ጠበባቸው ። ዳሩ ግን ጥቂት ካሰቡ በኋላ እቴጌይቱን ጠርተው ፣ ” እባክዎን በቁጥር ተጣልተናልና ይዳኙን ፣ አምስት መቶና አምስት መቶ ስንት ነው ? ቢሏቸው “ሺነዋ ! ” በማለት መለሱላቸው ። ” እግዜር ይስጥልኝ እመቤቴ ። እርስዎ ካዘዙኝማ ማለፊያ ነው “ ብለውም ወደጸዳጃ ቤት ሄዱ ።
ከዚያም እንደወጡ አንዱ መንገደኛ ” የኔታ የልደታ መንገድ በየት በኩል ነው ? ” ሲል ይጠይቃቸዋል ። “ በሱ አድርገህ ሂድ “
“ ይህስ ይዘቀዝቀኛል “
“ ከዘቀዘቀህማ ጨርቅህን አውልቅና ተንተራሰዋ !” ብለውት እርፍ ።
በማግስቱ ዘመድ ቤት ጠበል ይጠሩና ይሄዳሉ ፣ ቁጭ ብለው ጠላቸውን ሲጠጡም ሴትዬይቱ ከገንቦ ስትቀዳ ሲያመልጣት ሰምተው ኖሯል ። ይህን እያሰላሰሉ ሲጠጡ ሳለ ” ጠላ ልድገምዎት ? “ ብትላቸው ፣ ” እሺ እንደቅድሙ ጠረር አርገሽ ቅጂው ታዲያ “ አሏት ይባላል ።
የሰኔ ጾም እንደተፈታ ይቺው ዘመዳቸው ምሳ ትጋብዛቸውና ወደ መኖሪያዋ ይሄዳሉ ። ጥቂት እንደበሉም ወጡ ውስጥ ጥፍር አገኙበት። ጥፍሩንም ጠርገው እንዲታይ ለብቻው አስቀምጠው እጃቸውን ሰብስበው ቁጭ አሉ ። ሴትዬይቱ መብላት ማቋረጣቸውንም እንዳየች ” ይብሉ እባክዎ ፣ ጥሩ አይደለም እንዴ ? “ ብላ ብትጠይቃቸው ፣ ” አረ ጥሩ ነው ። ጥፍር ያስቆረጥማል “ አሏት ።
አለቃ ገብረሐና ( ምእራፍ ሁለት )
ቀልድ በዛ ፤ ስደት ተከተለ
የካቲት 5 ቀን 1847 ዓ. ም ደጃች ካሳ ” ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ “ ተብለው በጳጳሱ አቡነ ሰላማ ተቀቡ ። አባ ገብረሐናንም ቤተመንግሥት አገኙዋቸው ። አጼ ቴዎድሮስ አባን በምሁርነታቸው ቢወዷቸውና ቢያከብሩዋቸውም ቀልዳቸውና ፌዘኝነታቸውን ይጠሉ ነበር ። ዳሩ ግን ከልጅነት ጀምሮ እስከ ጎልማሳነት አብሮ ያደገ ልምድ ከተፈጥሮ ባህርይ የበረታ ነውና አባ ገብረሐና ቀልዳቸውን ፣ ምፀታቸውን ማቆም አልቻሉም ።
ለምሳሌ ፣ ብላታ አደጎ የተባለውን የቴዎድሮስ አሽከር ምንግዜም የሚጠሩት ብላታ አህዮ እያሉ ነበር ። ቴዎድሮስ “ ተው ገብረሐና ሰው እንዲህ አትዘርጥጥ “ ብለው ቢመክሯቸውና ቢገስጹዋቸው ፣ ” አባቱ ያወጣለትን ስም ኋላ ምን ላድርግ ? አድግ ማለት በግእዝ አህያ ማለት አይደልምን ? “ ብለው አሻፈረኝ አሉ ።
አንደዜም ከታላላቅ መኳንንት ጋር ሲጫወቱ የሴት ነገር ተነሳና አባ ሆዬ ” አንድ ቀን ከመኝታዬ ሌሊት ተነስቼ በጨለማ እየዳበስኩ ገረድ ስፈልግ የቤት ምሰሶ አገኘኝና ግንባሬን አለኝ “ ብለው ዋሽተው ያስቋቸዋል ። ይኸኔ አንዱ መኮንን “ አባ ቆመጥ ይዘው ምሰሶ ያለበትን እያወዛወዙ ቢሄዱ ኖሮኮ አይመታዎትም ነበር ” ብለው ቢስቁባቸው ፣ አጅሬ አብረው ስቀው “ ጌታዬም ለካ ይህን ያውቁ ኖሯል ? ” በማለት አሽሟጠጧቸው ። እንደዚህ እያደረጉ መኳንንቱን ሁላ በየጊዜው ሲነድፉት ቴዎድሮስ በድርጊታቸው አዝነው ፣ ” ገብረሐና ፍትሃነገሥቱን ጻፍ ፣ ፍርድም ስጥ ፣ ገንዘብም ያውልህ ፤ ቀልድህን ግን ተወኝ ተው ተመከር ! “ ብለው ተግሳጽም ምክርም ለግሰው እንደቀድሞው አቤቶ ምኒልክ አጠገብ እየተቀመጡ ግብር መብላታቸውን ቀጠሉ ።
ቴዎድሮስም ኢትዮጵያን የማዋሃዱንና ሕዝብ የማሰልጠኑን ተግባር ገፉበት ። ተክለጻድቅ መኩሪያ ይህንኑ እንደሚከተለው መዝግበውታል ። ” ሰው ሁሉ በእለት ተግባሩና በደመወዙ እንዲያድር እንጂ ባሪያን መሸጥ ወይም መሸፈት እንዳይኖር በጠቅላላው ገበሬም ወደርሻው ነጋዴም ወደንግዱ ፣ የቀረውም ሰው በየስራው እንዲመለስ ባዋጅ አስታወቁ ። በዚህ ጊዜ የቴዝባ አገር ሰዎች ቀርበው ጃንሆይ ሰውን ሁሉ በየሥራህ ግባ ካሉት እኛም ከሌብነትና ከሽፍትነት በቀር ሌላ ሥራ የለንምና ይኸንኑ ሥራችንን ይፍቀዱልን ሲሉ ጥቂት ሆነው አመለከቷቸው ። እርሳቸውም… እኔም ለራሴ ታማኝ ዘበኛ ለመቅጠር የምፈልገው እንደንንተ የዚህ ልማድ ያለውን ጠንካራ ሰው ነው ። ይሁን እንጂ አሁን ያላችሁት ጥቂቶች ናችሁና ፣ ሌላ ባእድ ሳትጨምሩ የዚህ ልማድ ያላቸውን ብቻ አጣርታችሁ ይዛችሁልኝ ኑ ብለው አሰናበቷቸው ።
በዚህ ጊዜ መኳንንቱ እንደዚህ ያሉትን ሌቦች መግረፍ ነበር እንጂ ፣ ማሰናበት እንዴት ይገባል ? እያሉ ሲያስቡ ፣ በተባለው ቀን ሌቦቹ ተሰብስበው ከፊታቸው ቆሙ ። አጼ ቴዎድሮስም እነሱ ብቻ መሆናቸውን ጠይቀው “ አዎን ጃንሆይ” ብለው ከመለሱላቸው በዃላ በዙሪያቸው የቆሙትን ወታደሮች አዘው በጥይት አንድ ሳይቀር አስደበደቧቸው ። ከዚያ ቀን አንስቶ በንጉሡ ፊት የሳቅና የቀልድ ንግግር በፍጹም ቀረ ይባላል ።፡”
አባ ገብረሐና ግን ሰውን መተንኮላቸውን አላቋረጡም ነበር ። በተለይ ብላታ አድጎን ያይሉባቸው ስለነበረ አድጎም አቤቱታቸውን ደጋግመው ማሰማት ቀጠሉ ። ቴዎድሮስ እንዲያ ተወጥረው ሳሉ የገብረሐና ጨዋታ ስላልጣማቸውም ፤ “ቆይ ይህን ደብተራ እሰራለት የለ ” ብለው ጊዜ ሲጠብቁላቸው ፣ አባ እንደልማዳቸው ብላታ አህዮ ብለው ተሳደቡና ተከሰው ቀረቡ ።
“ ለምንድን ሰደብኸው ? “
“ ጃንሆይ ! አህያ ሸራህያ እያልኩ ስጸልይ ሰምቶ “ ህ ” ን አጥብቆ አህያ ብሎ ሰደበኝ አለንጂ እኔ ፈጸሞ አልሰደብኩትም “
“ በሉ እንግዲህ ምላሱ ቀርቶ ታገሉና ወንዱ ይለይ ! “
አፈሊቅ አክሊሉ ገ/ ኪሮስ እንደሚሉት በዚህም ትግል ያሸነፉት አባ ገብረሐና ነበሩ ። ወ/ት ኤልሳቤጥ ገሠሠ ባቀረቡት ጥናት ላይ ግን በትግሉ ያሸነፉት ብላታ አድጎ ናቸው ። እንደተሸነፉም “ አሁንስ ማን ይበጀህ ? “ ብለው ቴዎድሮስ ቢጠይቋቸው ፣ “ ታዲያ ይሄማ ዱሮውንስ ያህያ ሥራ አይደለም ? “ በማለት መለሱ ። ንጉሡም ክፉኛ ተቆጡ ።
በአባ ገብረሐና ” አለመገራት “ ተስፋ የቆረጡት አጼ ቴዎድሮስ ከፊታቸው ይርቁላቸው ዘንድ አባን ትግራይ ክፍለሀገር የሚገኘው የጨለቆት ሥላሴ አስተዳዳሪ አድርገው ሾሟቸው ።
ይሁንና አጼ ቴዎድሮስ በሃያሉ ክንዳቸው ያላሸቋቸው መሳፍንትና ባላባቶች ማንሠራራት ጀመሩ ። ንጉሡ ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር የነበራቸው ግንኙነት መሻከርም ለአፈንጋጮቹ መጠናከር መልካም አጋጣሚ ሆነላቸው ። በትግሬ ደጃች በዝብዝ ካሳ ( አጼ ዮሐንስ) ፣ በላስታ ዋግ ሥዩም ጎበዜ ( አጼ ተክለጊዮርጊስ ) ፣ በሸዋ ምኒልክና ሌሎችም ባላባቶች ፣ ቀሳውስቱና ሹማምንቱ ሁሉ ተነሱባቸው ። አጼ ቴዎድሮስ የገነቡት ሁሉ እንደንቧይ ካባ ሲፈርስ ሲያዩም ክፉኛ ተበሳጩ ፣ ብዙ የጭካኔ ተግባርም ፈጸሙ ። በተለይ የካህናቱ መሠሪነት ስላበሳጫቸው ” ካንዱ አገር ወዳንዱ አገር ሲዘዋወሩ በከበሮ ፣ በጸናጽል ሊቀበላቸው የሚወጣውን ካህን ሁሉ እያስከበቡ በጥይት ያስደበድቡት ጀመር ። ጳጳሱንም በግዞት ወደመቅደላ ሰደዷቸው ። “ መንግሥታቸውን ለመገልበጥ ካህናቱ መዶለታቸውን እንዳወቁም ፣
“ ይህ አረግራጊ
አቴና ወጊ ፣
ራሱን ታጣቂ ፣
ወገቡን ሰባቂ ፣ ” እያሉ ካህናቱን በገሃድ ይዘልፉ ጀመር ።
ቴዎድሮስ እንዲገለበጡ ካሴሩት ቀንደኛ ካህናት አንዱ አባ ገብረሐና መሆናቸው እንደተደረሰበትም አባ ገብረሐና እንዲታሠሩ ንጉሡ አዘዙ ። ይህን የሰሙት ገብረሐናም ሸሽተው ዘጌ ገዳም ተደበቁ ። አባ ገብረሐና ዘጌ ገዳም ሁለት ዓመታት በስደት እንደተቀመጡም ይወሳል ። በዚህ ቆይታቸው ወቅት ረሃብ የገባና ይቸገራሉ ። አንድ ቀን ለወስፋት ማስታገሻ የምትሆን ቁራሽ ዳቦ ከአገልጋያቸው ጋራ ተካፍለው ከበሉ በኋላም ዲያቆኑ ተነስቶ ” ጌታዬ ስብሃት ልበል ? (ምስጋና ላቅርብ ) “ ቢላቸው ፣ ” ተው ልጄ ቀለዳችሁብኝ ብሎ ይቆጣል “ አሉት ይባላል ።
አንደዜ ደግሞ እዚያው ጎጃም እንዳሉ የንጉሥ ተክለሃይማኖት ወዳጅ ይሞታሉ ። ከቅዳሴ ውጭ ዜማውና ለቅሶው ቀልጦ ሳለ አንዱ ያገሬው ተወላጅ አባን “ ዜማው እንዴት ነው ? “ ብሎ ቢጠይቃቸው “ ካገራችሁ ደብተራስ ያገራችሁ አልቃሽ ትሻላለች ! ” ብለው መለሱለት ።
የረሃቡ ዘመን እንደተገባደደ አንዲት የጎጃም ሴት የቃና ዘገሊላን በዓል ምክንያት በማድረግ ጠበል ጠዲቅ እንዲቀምሱ ትጠራቸዋለች ። አባ ገብረሐና ጥሪውን አክብረው እንደ ደረሱ ሴትዬይቱ ጠላውን እየቀዳችላቸው ፣ “ አባቴ የችኮላ ሥራ ሆኖ ጠላው ቀጠን ብሏል “ ብትላቸው “ አዬ አካላቴ የምናከብረውስ የውሃ በዓል አይደል ? “ አሉዋት ይባላል ።
አባ ገብረሐና ይህን በሚፈጽሙበት ጊዜ አጼ ቴዎድሮስ አፈንጋጭ ባላባትና መሳፍንትን ለማስገበር ይሯራጡ ነበር ። ዳሩ ግን ኢትዮጵያን አዋህደው ታፍራና ተከብራ የምትኖር አገር ለማድረግ ያደርጉ የነበሩትን የተቀደሠ ተጋድሎ ሕዝቡ ስላልተገነዘበላቸው ከያካባቢው መኳንንት ጋራ በማበር አበሳጫቸው ። ይህ የጥፋት ጀሌ ይታረም እንደሁ ብለውም ብዙ ነፍስ አጠፉ ። ይኸኔ ወንድሟና አባቷ የተሰቀሉባት አንዲት ሴት የፈለጉትን ያድርጉኝ ብላ ፤
“….. አንድ እግር በርበሬ መንቀል አቅቷችሁ
አንድዶ ለብልቦ አቃጥሎ ይፍጃችሁ ?
ሺ ፈረስ ከኋላው ፣ ሺ ፈረስ ከፊቱ
ሺ ብረት ከኋላ ፣ ሺ ብረት ከፊቱ
ይህን ሳታይ ሞተች ኮሶ ሻጭ እናቱ ።
ይህንን ሲሰማ ያጎራል ላመሉ ፤
ማናትም ቢላችሁ ምንትዋብ ናት በሉ ” ስትል ገጠመች ።
የእንግሊዝ መንግሥት የሕዝቡን መበታተን እንዳወቀ ቴዎድሮስን እንዲይዙ ወታደሮቹን ላከ ። መኳንንቱ ፣ ባላባቱና አብዛኛው ሕዝብ የንጉሡን ክፉ ይመኝ ስለነበረም ያላንዳች ተቃውሞ ጠላትን ቴዎድሮስ ወደነበሩበት መራ ። ንጉሡም “ ከፉህላ ተነስተው የተረፋቸውን ጥቂት ወታደር አስከትለው እመቅደላ ምሽግ ገብተው በመድፍና በጥይት ከእንግሊዞች ጋር ጦርነት ገጠሙ ። በዚሁ ጦርነት ከእንግሊዝ የጦር ሠፈር የተተኮሰ የመድፍ ጥይት የነበሩበትን መዝጊያ ሰብሮ ጣለው ። እንግሊዞችም ይዘውት የነበረው መድፍና መትረየስ አዲስ የመጣ ስለሆነ የመድፉ ጥይት ተተኩሶ እመሬት ካረፈ በዃላ እንደገና እየፈነዳ የመጣውን ያህል ደግሞ እየሄደ ጠላትን የሚጎዳ ነበር ይባላል ። ቴዎድሮስ ባላቸው ኃይል ተዋግተው ድል ስለሆኑ ወታደሮቻቸውን ስመው እንግሊዞች ለመማረክ ታችኛውን በር ሰብረው እየተጋፉ ሲገቡ ንጉሡ ወደላይኛው በር አልፈው በገዛ ሽጉጣቸው ራሳቸውን ገደሉ ።” እንግሊዞችም እስረኞቻቸውን አስፈትተውና ያገኙትን ሁሉ ዘርፈው ወዳገራቸው ተመለሱ ። ሴረኛው ደብተራ ገብረሐናም ነጻ ወጡ ።
ከዚያ አዋቂ ሰው ወድቆ አይወድቅምና ልባቸው እንደፈቀደ ለመኳንንቱ እያደሩ ሲያገለግሉ ቆዩ ። በ1864 ዓ.ም. ግን ደጃች በዝብዝ ካሳ መሳፍንቱን ሁሉ አስገብረው ” ዮሐንስ አራተኛ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ “ ተብለው እንደተቀቡ አባ ገብረሐና ከጎንደር ሊቃውንት ጋር ወደትግራይ ሄዱ ። አካሄዳቸውም “ ንጉሡን እንኳን ዘመኑን ለወጠልዎ ! “ ለማለት ነበር ። ታዲያ መስከረም አሥር ቀን ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች እምነት መሠረት የአጼ መስቀል ምራት ነውና ይህንኑ በዓል ለማክበር ንጉሡ ባሉበት ከያገሩ የመጡት ሊቃውንት ተሰበሰቡ ። የአክሱም ሊቃውንት ምራቱን ለጎንደር እንስጥ የሚል ሃሳብ አቀረቡ ። ይኸኔ ላስቴው የድጓ መምህር የጌታ ጌጡ “ እኔ ሳለሁ አይመሩም “ ብለው ተነሱ ። ከዚያም የላስታዎች አፈጉባኤ መምህር ጌጡ ፣ የጎንደሮች አፈጉባኤ አባ ገብረሐና ሆነው ሙግት ገጠሙ ።
“ ተጠየቅ ፣ ገብረሐና “
“ ልጠየቅ “
“ እኔ ሥርወ መንግሥት መሆኔን አታውቅም ? “
በጊዜው “ ሥልጣን ወደላስታ የሄደው በንጥቂያ ነው “ የሚባለው ትውስ ያላቸው አባ ሆዬ ፣ ” እኔ ገብረሐና ጽድቅ የላሊበላ ፣ ዕድሜ የማቱሳላ ሲሉ እሰማለሁ እንጂ ያንተን ሥርወ መንግሥትነት አላውቅም “ አሏቸው ። አጼ ዮሐንስ ይቺን ሲሰሙ “ ጽቡቕ ነው ገብረሐና ። ጎንደር ይምራ “ ብለው ፈረዱላቸው ይባላል ። አንዴም ልክ እንደዚሁ በዮሐንስ ዘመነ መንግሥት ባደባባይ ክርክር ይነሳል ። ሁለት መሪ ጌታዎች ” እኔ ሳለሁ አትመራም ። የምራቱ ተራ የኔ ነው ። አረ ባምላኩ ፣ አረ ባምላኩ ! “ እያሉ ሲጯጯሁ አጼ ዮሐንስ ይሰሙና “ እኔ እያለሁ በዮሐንስ አምላክ ! ትላላችሁ እንጂ እንዴት ባምላኩ ትላላችሁ ?” ብለው ቢያፈጡባቸው ፣ አባ ገብረሐና “ ጃንሆይ ሌላም ነገር አይደል ሁለት ሰዎች በጩኸት ተጣልተውብን ነው “ በማለት ቁጣውን በፈገግታ ተኩት ። የምራቱም ሥርዓት ባግባቡ ተፈጸመ ።
አጼ ዮሐንስ ከፖለቲከኛነት ይልቅ ወደ ሃይማኖተኛነት ያዘነበሉ መሪ ስለነበሩ የኢትዮጵያን ሃይማኖት አንድ ለማድረግ ሲሯሯጡ መጋቢት ሁለት ቀን 1881 ዓ.ም. አለፉ ። የዮሐንስም ውጥን እንደቴዎድሮስ መና ሆኖ ቀረ ። አልቃሾችም ፤
” አጼ ዮሐንስ ሞኝ ናቸው
እኛም ሁላችን ናቅናቸው
ንጉሥ ቢሏቸው በመሃሉ
ወሰን ጠባቂ ልሁን አሉ ።
በደንቢያ መታረድ አዝኖ ዮሐንስ
ደሙን አፈሰሰ እንደ ክርስቶስ ።
የጎነደር ሃይማኖት ቆማ ስታለቅስ
አንገቱን ሰጠላት ዳግማይ ዮሐንስ “
ብለው ሙሾ ደረደሩላቸው ።
አለቃ ገብረሐና ( ምእራፍ ሶስት )
ከስደት ወደቤተ መንግሥት
አጼ ዮሐንስ በሞቱ በስምንተኛው ወር የቀድሞው የአጼ ቴዎድሮስ ምርኮኛ አቤቶ ምኒልክ በምድረ ኢትዮጵያ የሚያስፈራቸው ኃይል እንደሌለ አስረገጡ ። ጥቅምት ሃያ አምስት ቀን 1882 ዓ.ም “ ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ “ ተብለውም ተቀቡ ። በዚህ ጊዜ አባ ገብረሐና ጎንደር የሚገኘው የአቡነ ሐራ ገዳም አስተዳዳሪ ሆነው ይሠሩ ነበር ። ጥቂት ዓመታት እንዳገለገሉም ድርቅ ገብቶ የአገሩ ሕዝብ ተራበ ። የገዳሙ አስተዳዳሪ የሆኑት አባ ገብረሐናም ከተሰበሰበው የስለት ገንዘብ አንድ ሺውን አንስተው ለባላገሩና ለካህናቱ አከፋፈሉ ።
Read More
ወዲያውኑ ካህናቱ “ አስተዳዳሪያችን በሺ የሚቆጠር ብር በልተውብናል “ ሲሉ አዲሳባ አፈንጉሥ ነሲቡ ዘንድ ይከሱዋቸዋል ። አፈንጉሥ ነሲቡም ባስቸኳይ የማዘዣ ወረቀት ጽፈው ወዳዲሳባ እንዲመጡ ያደርጋሉ ። እንደደረሱም አጋፋሪው “ አባ ገብረሐና መጥተዋል “ ሲል ፣ “ እኛ ቀልደኛው ናቸው ? “ በማለት አፈንጉሥ ቢያንጓጥጧቸው ፣ አባ ፈጠን ብለው “ ብሉይና ሐዲስማ በነሲቡ ይፈተታሉዋ ( ይተረጎሟሏ ) “ ሲሉ መለሱላቸው ። ክርክሩ እንደተጀመረም ፣ ” ገንዘቡን ማጥፋትዎን አያምኑምን ? “ ብለው ጠየቋቸው ። “ በርግጥ ለነዳያን የሚሰጠውን አውጥቼ ሰጥቼያለሁ ፣ ለመስዋእት የሚውለውንም እንዲሁ ፣ የተረፈውን ግን ፍትሃነገሥት በሚያዘው መሠረት ለማኅበሩ ሰጥቼ ተካፍለውታል ።”
” እንግዲያውስ ያጠፉትን ገንዘብ መክፈልዎ አይቀርም ። “
” ታዲያ እኔ ገብረሐና ምን ይመጣብኛል ብለው ነው ? እንደምጥዋ እቃ በነሲብ አልሸጥ ። “
” አጋፋሪ ዝም ትለኛለህ ። ወስደህ ቀፍድድልኝ እንጂ ! ሲሉ አፈንጉሡ በደም ፍላት አዘዙ ።
እንዳጋጣሚ ግን የምኒልክ የልፍኝ አሽከር ራስ አባተ ችሎት ተገኝተው ኖሮ “ አፈንጉሥ ምንም እኔ እንኳን ባላውቃቸው ጃንሆይ የኒህን ሰው ክብር ሲናገሩ ሰምቻለሁና ትጣላላችሁ “ ሲሉ ያስጠነቅቋቸዋል ።
“ ታዲያ ምን ይሻላል ? “
“ ጃንሆይ ይፍረዱባቸው ። “
በዚሁ ተቆረጠና ተከሳሹ ገብረሐና ምኒልክ ችሎት ቀረቡ ። አፈንጉሥም የወንጀሉን ይዘት ለንጉሡ ሲያስረዱ “ እኒህ ቄሶች አስተዳዳሪው የገዳማችንን ገንዘብ በልቶብናል በማለት ከሰውት እሱም መብላቱን አምኗል ። ሆኖም ክፈል ብለው “ በክፉ ቀን ለሕዝብ አካፍየዋለሁ ብሎ መልስ ሰጥቷል “ እንዳሉ ፣ ዳግማዊ ምኒልክ አፈንጉሡ የጀመሩትን ሳያስረጨርሷቸው ካፋቸው ነጥቀው ፣ “ አንተ የምትለው እሳቸውን ነው ? “ ብለው ገሰጹአቸው ። ከዚያም ወዳአባ ገብረሐና ዘወር ብለው “ ጌታ አባ ገብረሐና ፍትሃነገሥቱን አዋቂ አልነበሩምን ? ምን ነካዎ ? ” በማለት ቢጠይቋቸው ፣ “ ፍትሃነገሥቱማ ከገባው ብጻት ሲሶው ለካህናት ፣ ሲሶው ለሠራያን ሊሰጥ ይገባል ይላል ። ስለዚህም ክፉ ቀን ቢሆን እኔም ለሕዝቡ አካፈልኩት ። አቡነ ሐራ እንደሁ አባታቸውን አይጦሩበት ፣ ልጃቸውን አይድሩበት ፣ ታዲያ ገንዘቡ ተቀምጦ ምን ይሆናል ብዬ ነው ጃንሆይ ” ሲሉ አብራሩ ።
“ አበጀህ ፣ ቀድሞውኑስ የተማርክም አይደለህ “ ብለው ምኒልክ ፍርዱን አጸኑላቸውና በነጻ አሰናበቷቸው ። ከዚያም የቀድሞው ራጉኤል አካባቢ ቤት አሠርተውላቸው አቋቋምና መርገድ እያስተማሩ እንዲቀመጡ ለመኗቸው ። አባ በሐሳቡ ስለተስማሙ እውቀታቸውን እያካፈሉ መኖር ጀመሩ ። እንጦጦ ( ቀድሞ ዲልዲላ ይባል የነበረው አካባቢ ) በ1875 ዓ.ም. የተተከለው ራጉኤል ቤተክርስትያን ውስጥም በስፋት ማስተማር ቀጠሉ ። አጼ ምኒልክም እለት ፣ እለት ቅቤውን ማሩን ፣ ቡልኮውን ይልኩላቸው ነበር ። እንዲያም ሆኖ የእንጦጦን ብርድ ያልቻሉት አባ ገብረሐና ፣ “ የእንጦጦን ብርድ የለመደ ሲኦልን አይሰቀቃትም ” ይሉ ነበር ይባላል ። ምኒልክ አንደዜ ራጉኤልን ሊሳለሙ ቢመጡ አባ ቡልኳቸውን ተከናንበው ዳዊት ሲደግሙ ስላዩ ቢስቁባቸው ገብረሐና ሆዬ “ ጃንሆይ ጋሪ ቡልተኒ “ ብለው በደንብ አሳቋቸው ።
አባ ገብረሐና በልቶ ጠጥቶ መተኛትን እንጂ ትምህርት የማይወድ ሰነፍ ተማሪ ነበራቸው ። ታዲያ አንድ ጊዜ ጠርተውት “ እስቲ ይህን ምእራፍ ውጣው “ ብለው አዘዙት ። ተማሪውም እንደምንም አምታቶ ጨረሰና ፣ ” የኔታ ጨረስኩ። ጎበዝ አይደለሁም ? “ ብሎ ቢጠይቃቸው ፤ “ እንዴታ ጎበዝ እንጂ ያውም ብላተኛ አሉት ይባላል ።
ከጥቂት ቀናት በኋላ አባ ገብረሐና ግብር እንዲበሉ ይጠሩና ቤተመንግሥት ይመጣሉ ። ይሁን እንጂ ከመኳንንቱና ካህናቱ ጋር እየተጋፉ ሲገቡ አንድ የማያውቃቸው ከልካይ በቀጨሞ ዠለጣቸው ። እንደምንም ብለው ከገቡ በዃላ ግን እልህ ስለያዛቸው ምግቡንም መጠጡንም አልበላ አልጠጣ አሉ ። “ ምን ሆነሃል ገብረሐና ? ” ብለው ምኒልክ ቢጠይቋቸው ፣ “ ትንሽ ቀጨሞ ስለቀመስኩ ነው ፣ ጃንሆይ “ በማለት መለሱላቸው ።
የኔታ ገብረሐና አጭር ፣ ድምፀ መልካምና መልከ ቀና መነኩሴ ነበሩ ይባላል ። በቁመታቸውም ማጠር የተነሳ የሚጠቀሙባት ጭራ ትንሽ ነበረች ። በጊዜው ትልቅ ጭራ ማንከርፈፍ የጨዋነት መለኪያ ሆኖ ይቆጠር ነበርና አንዱ ግዙፍ መኮንን ፣ “ እንዴት እርስዎን የሚያክል ሰው ይቺን ቆራጣ ጭራ ይይዛል ? ለእርስዎ የምትገባ አይደለችም ” ቢላቸው ፣ “ ለኔ ፊት እንደሁ ትበቃኛለች ። ደንቢያ አልከለክልባት “ ሲሉ መለሱላቸው ።
አባ ወዳገራቸው መመለስ እንዳሰቡ ልብስ እንዲሰሩላቸው ከሸማኔዎች ጋር ይዋዋላሉ ። ከጥቂት ቀናት በኋላም በበቅሎ ታጅበው ወደቤተመንግሥት ሲወርዱ ሸማኔዎች እንዳዩዋቸው “ ጃንሆይ የሚያከብሯቸው ቄስ መጡ “ ብለው ፈጥነው ሲነሱ አንዱ አመለጠው ። ይኸኔ አባ “ ልብሴን እስካሁን ሳትሠሩልኝ መቆየታችሁ ሲገርመኝ አሁንማ እስከመቋጠሩም ተዋችሁታ ! “ አሉዋቸው ።
ሊቀ ገብረሐና ቀሳውስቱንና ዲያቆናቱን ከማስተማር በተጨማሪ ሥራዓተ ቤተክርስቲያንንና ሥርዓተ ቤተመንግሥትንም ለዳግማዊ ምኒልክ ያስጠኑ ነበር ። በዚህ ዓይነት አዲስ አበባ ከቆዩ በኋላ ንጉሡን ተሰናብተው ወደጎንደር ጉዞ ጀመሩ።

November 23, 2009 at 11:11
As an Ethiopian Citizen it lovely to read about Sir. G/Hanna. I love Enemamar Just give as more jokes. Thank you.
March 9, 2010 at 13:54
It is beyond joke. It shows that amharic is wealthy in meaning. Please do more.
April 18, 2010 at 12:54
Awesome !!! I strongly encourage you
Keep it up
Love to visit Enemamar
August 7, 2010 at 06:58
temechegn